Blog Archive

Saturday 13 September 2014

3. ታቦት በዮሐንስ ራእይ

3. ታቦት በዮሐንስ ራእይ

pdf version
እንግዲህ በሁለቱ ኪዳኖች መካከል ያሉት መሠረታዊ ልዩነቶች ግልጽ ከሆኑልን፤ በመጀመሪያ ወደ ተነሳንበት የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ እንመለሳለን።

የዮሐንስ ራእይ
1119በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።

ይህ ክፍል በአንዳንዶች ላይ ጥያቄና ግራ መጋባት ሲፈጥር ይታያል። በአዲስ ኪዳን የታቦት አገልግሎት ሳይጠቀስ ቆይቶ ድንገት በራእይ መጽሐፍ ላይ የብሉይ ኪዳኑ ታቦት ሲጠቀስ ትንሽ ግር የሚላቸው ሰዎች አሉ።

በዚህ ክፍል የብሉይ ኪዳኑ ታቦት መጠቀሱ ለምንድነው? ክፍሉስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት ምንድነው? የክርስቶስ ተከታዮች እንደ ብሉይ ኪዳን አይነት ታቦት ሠርተው የብሉዩን ሥርዓት እንዲያካሂዱ ነው የሚያስተምረው ይህ ክፍል? አይደለም። የክርስቶስ ተከታዮች ወደ ብሉዩ ኪዳኑ ሥርዓት ይመለሱ ወይም የብሉዩንና የአዲሱን ሥርዓት ጎን ለጎን ያካሂዱ የሚል መልዕክት ነው በዚህ ክፍል ያለው? ይህን የሚያሳይ አንዳችም ነገር በዚህ ክፍል የለም። እንዲህማ ቢሆን አዲስ ኪዳንም ባላስፈለገ ነበር። ሁለቱን ኪዳኖች ጎን ለጎን በማካሄድ በሁለቱም በኩል ለመጽደቅ እንደማይቻልም ሁሉ ተመልክተናል፤ ስለዚህ ይህ ክፍል አዲስ ኪዳን ደጋግሞ ያስተማረውን ትምህርት የሚቃረን ወይም የሚገለብጥ ትምህርት ጨርሶ የለውም።

ታዲያ በዚህ ክፍል የታቦቱ መታየት ለምን አስፈለገ? ሊስተላለፍስ የተፈለገው መልዕክት ምንድነው? የዚህን ክፍል መልእክት ከመመልከታችን በፊት ስለ ዮሐንስ ራእይ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን እንመልከት።

አንደኛ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ የትንቢት መጽሐፍ ነው።

የዮሐንስ ራእይ 1
1 ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ 2 እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ። 3 ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃልየሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።

ይህም ማለት እንደ ብሉይ ኪዳን የትንቢት መጽሐፍት ሁሉ ይህም የዮሐንስ ራእይ በአብዛኛው ወደፊት ሊመጣ ስላለውም ነገር የሚተነብይ መጽሐፍ ነው።

የዮሐንስ ራእይ 1
19 እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ።

የዮሐንስ ራእይ እንግዲህ አሁን ስላለው ወይም ዮሐንስ በጻፈበት ጊዜ ስለነበረው ብቻ ሳይሆን ወደፊት ስለሚሆነውም የሚተነብይ መጽሐፍ ነው። እንዲያውም ከምዕራፍ 4 ጀምሮ ያለው ክፍል ወደፊት ሰለሚሆነው የሚተነብይ ስለወደፊት የሚናገር ትንቢት እንደሆነ በግልጽ ተጠቅሶአል።

የዮሐንስ ራእይ 4
1 ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ። ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ።

ስለዚህ መነሻ የሆነን በምዕራፍ 11 የሚገኘው ጥቅስ የሚናገረው ወደፊት ስለሚሆን ትንቢት እንደሆነ በመጀመሪያ መረዳት ይገባናል።

ሌላው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ብዙ ምሳሌያዊ ምልክቶችን (symbols) ያካተተ መጽሐፍ መሆኑን ማወቅ መጽሐፉን በሚገባ ለመረዳት ይጠቅመናል። ነገር ግን ምሳሌያዊ ምልክቶቹን ራሳችን እንደፈለግንና እንደመሰለን የምንተረጉመው ሳይሆን የምልክቶቹ ተርጓሚ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ መረዳት አለብን።

የዮሐንስ ራእይ የትንቢት መጽሐፍ እንደመሆኑ መጽሐፉን በይበልጥ ለመረዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተነገሩ ትንቢቶች መሠረታዊ መረዳት ሊኖረን ይገባል። በዚህ ጽሑፍ የተነሳንበትን ክፍል ለመረዳት የሚያስችለንን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ብቻ በአጭሩ እንመለከታለን።

የዮሐንስ ራእይ የሚናገራቸው የወደፊት ትንቢቶች በአብዛኛዎቹ በብሉይ ኪዳን ዘመን በነበሩ ነብያትም የተተነበዩ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ዮሐንስ ራእይ ከምዕራፍ 6 እስከ ምዕራፍ 19 ያለው ክፍል በዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ ስለተነገረው ሰባኛው ሱባዔ ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ከመምጣቱ በፊት ስለሚሆነው ስለ መጨረሻው የሰባት ዓመት ታላቁ የመከራ ዘመን የሚናገር ነው። በተለይ ደግሞ ከሰባት ዓመቱ አጋማሽ ጀምሮ ማለትም በተቀሪዎቹ ሶስት ዓመት ተኩል ጊዜያት እጅግ ታላቅ መከራ በምድር ላይ እንደሚሆን ጌታም ታናግሮአል።

የማቴዎስ ወንጌል  24
21 በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።
22 እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።

በመከራው ዘመን ይሆናሉ ተብለው በብሉይም በአዲስም ከተተነበዩት ትንቢቶች አንዱ የእስራኤል ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ወደ አዲሱ ኪዳን መግባትን የሚናገር ትንቢት ነው።

ትንቢተ ሕዝቅኤል  20
33 እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦ 34 ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። 35 ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። 36 በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦ 37 ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ 38 ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

በዚህ ክፍል ልክ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ምድር አውጥቶ በምድረበዳ ፊት ለፊት ከእነርሱ ጋር እንደ ተፋረደና ወደ ብሉዩ ቃል ኪዳን እንዳስገባቸው እንዲሁ እንደገና እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በምድረበዳ ፊት ለፊት እንደሚፋረድና ወደ አዲሱ ኪዳን እንደሚያስገባቸው የተነገረ ትንቢት ነው። "ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ" ቁጥር 37። እግዚአብሔር እንግዲህ እስራኤልን ወደ አዲሱ ኪዳን የሚያስገባቸው ልክ ወደ ብሉዩ ኪዳን እንዳስገባቸው አይነት በምድረበዳ ከሕዝቡ ጋር ፊት ለፊት በመፋረድ ነው። በሮሜ 11 ላይም የእስራኤል ሕዝብ የተላከላቸውን መሲሕ አሁን መቀበል እንዳልቻሉና በመንፈሳዊ እንቅልፍ ውስጥ እንዳሉ ነገር ግን ወደፊት ሕዝቡ ክርስቶስን እንደ መሲሕአቸው እንደሚቀበሉና እንደሚድኑ በስፋት ተብራርቶአል።

እንግዲህ በራእይ መጽሐፍ ወዳለው ወደ ተነሳንበት ጥቅስ ስንመለስ ይህንን የተነሳንበትን ጥቅስ በሚገባ ለመረዳት ጥቅሱ የሚገኝበትን ምዕራፍ 11 እና ምዕራፍ 12ን በሙሉ መመርመር ይገባል። በተለይ ከምዕራፍ 11፤15 ጀምሮ ማለትም ሰባተኛው መልአክ መለከት ከነፋ በኋላ እስከ ምዕራፍ 12 መጨረሻ ያለው የተያያዘ ሃሳብ ነው። በዚህም ክፍል ከታቦቱ ጋር ተያይዛ በቀጣዩ በምዕራፍ 12 የተጠቀሰች አንዲት ሴት አለች። ወደ ታቦቱ ከመምጣታችን በፊት ከታቦቱ ጋር ተያይዛ በተከታታይ ስለተጠቀሰችው ስለዚች ሴት በመጀመሪያ እንመልከት።

ይህች ሴት በምዕራፍ 11 የመጨረሻ ጥቅስ ከሆነው ከታቦቱ ጥቅስ ጋር አብራ ተያይዛ ከምዕራፍ 12 ቁጥር 1 ጀምሮ የተጠቀሰች ናት። እርሷም ከታቦቱ ጥቅስ ጋር ወዲያው ተከትላ የተገለጸች ሴት ስለሆነች የእርሷን ማንነት መረዳት ታቦቱ ለምን እዚህ ክፍል ላይ እንደተጠቀሰ እንድንረዳ ያግዘናል።

(የዮሐንስ ራእይ 11) 19በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ። (የዮሐንስ ራእይ  12) 1 ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። 2 እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች። 3 ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥ 4 ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። 5 አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። 6 ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች። 7 በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ 8 ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። 9ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።

በዚህ ክፍል ቁጥር 1 ላይ ስለ ሴቲቱ  መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር "ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ" ብሎ ይጀምርና የታየው ምልክት ምን እንደሆነ ሲገልጽ "ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች" ይላል። ስለዚህ ይህች ሴት ስለ አንድ ነገር የምታመለክት ምልክት (symbol) ናት ማለት ነው። መጽሐፍ ቁዱስ ራሱ ምልክት እንደሆነች ይናገራልና።

ሴቲቱ ወይም ሴትዮዋ ምንን እንደምታመለክት ወይም ትርጉሟ ምን እንደሆነ ለመረዳት የተገለጸችበትን ዓረፍተ ነገር እንመልከት። ሴቲቱ ፀሐይ እንደተጎናጸፈች፤ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች እንዳላትና በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የነበራት ሴት እንደሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህች ሴት እንግዲህ በፀሐይ በጨረቃና በአሥራ ሁለት ክዋክብት የምትመሰል ሴት ናት። ይህ ሴቲቱ የተገለጸችበት አገላለጽ ዘፍጥረት ላይ ዮሴፍ ካለመው ሕልም ጋር ተመሳሳይ ነው።

ኦሪት ዘፍጥረት
9 ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥እንዲህም አለ፦ እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትምሲሰግዱልኝ አየሁ። 10 ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው አባቱም ገሠጸው፥ እንዲህም አለው፦ ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህምመጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?

ይህ ክፍል ግልጽ እንደሚያደርገው ፀሐይና ጨረቃ አሥራ ሁለቱም ክዋክብት ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ ምልክቶች ናቸው። አሥራ ሁለቱ ክዋክብት የእስራኤልን ሕዝብ አሥራ ሁለት ነገዶች ፀሐይና ጨረቃ ደግሞ የነገዶቹን አባትና እናት የሚያመለክቱ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦአል። ያዕቆብ የእስራኤል ሕዝብ አባት እንደሆነና "እስራኤል" የሚለው ስም ራሱ እግዚአብሔር ለያዕቆብ ያወጣለት ስም እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዘፍጥረት  32፣27-28)። የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች አባቶች ዮሴፍን ጨምሮ አሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንደሚተረጉመው ይህቺ ሴት እንግዲህ የእስራኤልን ሕዝብ የምታመለክት ናት።

ሌላው ስለዚህች ሴት በቁጥር 5 የተጠቀሰው ነገር አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ እንደ ወለደች እና ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ እንደተነጠቀ ነው። አሕዛብን በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውና ወደ እግዚአብሔር ዙፋን የተነጠቀው ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ አያጠያይቅም። ክርስቶስም ከእስራኤል ሕዝብ ስለተወለደ ይህን ወንድ ልጅ የወለደችው ሴት የእስራኤልን ሕዝብ እንደሚያመለክት ሁለተኛው ማረጋገጫ ነው።

ወደ ሮሜ ሰዎች  9
4 እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ 5 አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።

ሌላው ከሴትዮዋ ጋር አብሮ በራእይ 12፣7 ላይ የተጠቀሰው የእግዚአብሔር መልአክ ሚካኤል ስለ ሴትዮዋ ማንነት ሌላ ፍንጭ የሚሰጠን ነው። ምክንያቱም ሚካኤል የእስራኤል ሕዝብ መልአክ እንደሆነ በትንቢተ ዳንኤል ተጽፎአልና።

ትንቢተ ዳንኤል 12
1 በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።

እንግዲህ ከላይ ካየናቸው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ መሠረት ካደረጉ ትርጉሞች እንደምንረዳው ከታቦቱ በመቀጠል ወዲያው የተጠቀሰችው ሴት የምታመለክተው የእስራኤልን ሕዝብ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ከላይ በሕዝቅኤል  20 ላይ እንደተመለከትነው እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ወደ በረሃ አውጥቶ በዚያ እንደተፋረዳቸውና ወደ ብሉዩ ኪዳን እንዳስገባቸው እንዲሁ እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ ከተበተኑበት አገሮች ከተሰበሰቡ በኋላ በምድረበዳ ፊት ለፊት እንደሚፋረዳቸውና ወደ አዲሱ ኪዳን እሥራት ውስጥ እንደሚያስገባቸው ተመልክተናል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብጽ እንዳወጣቸውና ከፈርዖን እንዳዳናቸው ሲናገር በዘጸአት ላይ እንዲህ ብሎ ነው የሚገልጸው።

ኦሪት ዘጸአት
194 በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል።

በዚህም በራእይ ምዕራፍ 12 ላይ ተመሳሳይ ነገር ነው የምንመለከተው።

የዮሐንስ ራእይ  12
6 ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች።
14 ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎችተሰጣት።

ሴቲቱ ከዘንዶው ማለትም በቁጥር 9 ላይ ማንነቱ እንደተገለጸው ከሰይጣን እንድታመልጥና "በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ" እንድትሸሸ "ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች" እንደተሰጣት እናነባለን። ይህም ልክ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከፈርዖን እጅ እንዳስጣላቸው እንዲሁ በታላቁ መከራ ዘመን እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ዘንዶው ከሚያስነሳባቸው ስደት እንደሚያስመልጣቸው የሚያመለክት ነው።

የሴቲቱ ሽሽትም ከሰባቱ ዓመት የመከራ ዘመን የመጨረሻውን አጋማሽ ማለትም ለሶስት ዓመት ተኩል እንደሆነም ተገልጾአል። ቁጥር 6 ላይ "ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን" ብሎ ሲጠራው ቁጥር 14 ላይ ደግሞ "ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ" ይለዋል። ማለትም አንድ አመት፥ ሁለት ዓመትና ግማሽ አመት ማለት ነው።

እንግዲህ በዚህ በሽሽት ዘመንና በበረሃ ነው እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ልክ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሁሉ ፊት ለፊት ተገልጦ ከተፋረደ በኋላ ወደ አዲሱ ኪዳን የሚያስገባቸው።

ምዕራፍ 12 ከመጀመሩ በፊት የታቦቱ መታየት እንግዲህ አሁን ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል። አንደኛ ቀድመን እንዳጠናነው ታቦት በእግዚአብሔርና በእስራእል ሕዝብ መካከል የተደረገው የብሉዩ ቃል ኪዳን ምስክር ነው። ይህ የቀድሞው ኪዳን ደግሞ ሌሎችን ሕዝቦች ሳይሆን እስራኤልን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነ ተመልክተናል። ይሄንንም የብሉዩን ኪዳን እስራኤል ባለመጠበቃቸውም ምክንያት አዲስ ኪዳን እንዳስፈለገም አይተናል። ስለዚህ በዮሐንስ ራእይ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝቡን ከመፋረዱ በፊት ማለትም ከምዕራፍ 12 በፊት እና በምዕራፍ 11 መጨረሻ የታቦቱ መታየት እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የሚፋረድበትና ወደ አዲሱ ኪዳን የሚያስገባበት ጊዜ መድረሱን የሚያመለክት ነው። ምዕራፍ 12 ደግሞ የእስራኤል ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን የብሉዩን ኪዳን እንዳልጠበቁ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር በበረሃ ተፋርዶ በሕዝቅኤል እንደተተነበየው ወደ አዲሱ ኪዳን የሚይስገባበትን ቅድመ ሁኔታ የሚያሳይ ነው።

ቀደም ብለን እንዳየነው በመጽሐፍ ቅዱስ ታቦት ሲጠቀስ ያን በሲናና ተራራ የተፈጸመውን ቃል ኪዳን የሚያመለክት ነው። ይህም የቃል ኪዳኑ ተጋቢዎች የሆኑትን እግዚአብሔርንና የእስራኤል ሕዝብን እንዲሁም የቃል ኪዳኑ የውል ስምምነት የሆነውን ሕጉን እንደሚያስታውስ አይተናል።

በዚህ በራእይ ላይም ታቦት ያንን በሲና ተራራ የተደረገውን የብሉዩን ኪዳንና የስምምነቱ አካል የሆኑትን እግዚአብሔርን፣ የእስራኤልን ሕዝብና ሕጉን የሚያመለክት ነው። እንዲያውም ከታቦቱ ጋር አብረው በዚህ በራእይ የተጠቀሱት "መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ" ወዘተም እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የብሉዩን ቃል ኪዳን ሲገባ በሲና ተራራ የሆነውን ሁኔታ የሚያስታውሱ ናቸው።

የዮሐንስ ራእይ
1119በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።

ኦሪት ዘጸአት  19
16 እንዲህም ሆነ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ። 17 ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው ከተራራውም እግርጌ ቆሙ። 18 እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር
ስለዚህ እንደ ብሉይ ኪዳኑም ይህም ታቦት የተጠቀሰበት የራእይ ክፍል እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያለውን ጉዳይ የሚያሳይ፤ የእስራኤልን የወደፊት ዕጣ የሚመለከት ነገር ነው እንጂ የክርስቶስ ተከታዮች በአዲስ ኪዳን ልክ እንደ ብሉይ ኪዳን የታቦት አገልግሎት እንዲጀምሩ የሚያስተምር አይደለም።

No comments:

Post a Comment