Blog Archive

Saturday 13 September 2014

1. የብሉይ ኪዳንና የታቦት አመጣጥና ምንነት

1. የብሉይ ኪዳንና የታቦት አመጣጥና ምንነት

pdf version
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ከአንዳንድ ወገኖች የሚደርሰን ጥያቄ ነው። ጥያቄውም ታቦትን የተመለከተ ሲሆን፤ በተለይ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ላይ ታቦት መጠቀሱ አንዳንዶች ላይ ጥያቄ መፍጠሩ አልቀረም። ታቦት በዮሐንስ ራእይ ከተጠቀሰ ታዲያ በአዲስ ኪዳንም ያስፈልጋል ማለት ነው? በዮሐንስ ራእይ ላይ መጠቀሱስ ምን ያስተምረናል ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ። ከዚህ በመቀጠል በታቦትና በአዲስ ኪዳን ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአጭሩ ለመመልስ እንሞክራለን።

በአዲስ ኪዳን ታቦት ያስፈልጋል ወይም አይስፈልግም የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስለ ታቦት ምንነት ትንሽ እንመልከት።

የታቦትን ወይም መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛው እንደሚጠራው "የኪዳን ታቦት" ወይም "የምስክር ታቦት"ን ምንነት በሚገባ ለመረዳት ደግሞ ታቦቱ የተሰጠበትን የብሉዩን ቃል ኪዳን መረዳት ያስፈልጋል። ታቦት ወይም "የቃል ኪዳን ታቦት" እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በሙሴ በኩል የገባው የቃል ኪዳኑ ምልክትና ምስክር ነው። ስለዚህ የኪዳኑን ታቦት ምንነት ለመረዳት ኪዳኑን ወይም ቃል ኪዳኑን ራሱን መረዳት ያስፈልጋል።

ብሉይ ኪዳን (የቀድሞው ኪዳን)


እግዚአብሔር የቃል ኪዳን አምላክ ነው። በተለያዩ ጊዜያት እግዚአብሔር ከግለሰቦችና ከእስራኤል ሕዝብም ጋር ቃል ኪዳን ገብቶአል። ከግለሰቦች ጋር ከገባቸው ቃል ኪዳኖች ውስጥ ከኖህ፤ ከአብርሃምና ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ደግሞ ሕዝቡን ከግብጽ ባርነት ነጻ ካወጣቸው በኋላ በምድረበዳ በሲና ተራራ የገባው ቃል ኪዳን ማለትም ብሉይ ኪዳን ወይም የቀድሞው ኪዳን የሚጠቀስ ነው።

ቃል ኪዳን ማለት በሁለት ሰዎች ወይም በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል የሚገባ የስምምነት ውል ነው። ስለዚህ የብሉዩንም ይሁን የአዲሱን ቃል ኪዳን ለመረዳት የስምምነቱ ውል ይዘት ምን እንደሆነና ቃል ኪዳን ተጋቢዎቹስ እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል። ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ግልጽ ከሆነልን በብሉይና በአዲስ ኪዳን ልዩነት ዙሪያ የምንጠይቃቸው ብዙ ጥያቄዎቻችን ይመለሱልናል።

መጽሐፍ ቅዱስ በኦሪት ዘጸዐት ከምዕራፍ 19-24 ላይ ስናነብ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር እንዴት ብሉይ ኪዳንን እንደሰጣቸው ወይም ከእነርሱ ጋር እንዴት ቃል ኪዳን እንዳደረገ እንመለከታለን።

በመጀመሪያ በምዕራፍ 19 ላይ እግዚአብሔር ራሱ በሲና ተራራ ላይ እንደወረደና በቀጥታ እንደተናገራቸው እናያለን።

ኦሪት ዘጸአት  19
በሦስተኛውም ወር የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ አለው። ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር። በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። 5 አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ 6 እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።

ኦሪት ዘጸአት  19
16 እንዲህም ሆነ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ። 17 ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው ከተራራውም እግርጌ ቆሙ። 18 እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር። 19 የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት።

እግዚአብሔር እንደዚህ በነጎድጓድና በመብረቅ ድምጽ በምድርም መናወጥ በሲና ተራራ ለእስራኤል ሕዝብ ከተገለጠ በኋላ በምዕራፍ 20 አሥርቱን ትዕዛዛት ለሕዝቡ ይሰጣቸዋል። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ይህ ቃል ኪዳን ወይም ብሉይ(የቀድሞ) ኪዳን ያካተተው አሥርቱን ትዕዛዛት ብቻ አይደለም። አሥርቱን ትዕዛዛት ጨምሮ ከምዕራፍ 20 እስከ ምዕራፍ 23 ያሉትን የተለያዩ ሕጎችን ሁሉ ያካተተ ነው። ከምዕራፍ 20 እስከ ምዕራፍ 23 ብዙ ሕግጋትን ሕዝቡ እንዲጠብቁ እግዚአብሔር ከነገራቸው በኋላ ሕዝብም እነዚህን ሕግጋት እንደሚጠብቁ ቃል ገብተው ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ያደርጋሉ።

ኦሪት ዘጸአት  24
3 ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ። እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። 4 ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ። 5 የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤልን ልጆች ጐበዛዝት ሰደደ። 6 ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው። 7 የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው እርሱም፦ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ። 8 ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ።

በዚህ ክፍል እንግዲህ እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር "ብሉይ ኪዳን" ወይም የቀድሞው ኪዳን ተብሎ የሚጠራውን ቃል ኪዳን ሲገባ እንመለከታለን።

የቃል ኪዳኑ ተጋቢዎች


በመጀመሪያ በዚህ በዘጽአት እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ባጠቃላይ የምንመለከተው የብሉዩ ቃል ኪዳኑ የተፈጸመው በእግዚአብሔርና በእስራእል ሕዝብ መካከል ነው።

ኦሪት ዘጸአት  19፤3
... ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር

ይህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ከግብጻዊያን ወይም ከኢትዮጵያውያን ወይም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር የገባው ቃል ኪዳን አይደለም። ይህ እግዚአብሔር ፊት ለፊት ተገልጦ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ኪዳን ነው። ተሰድደው ወደ እስራኤል አገር ምጻተኛ (ስደተኛ) ሆነው ከሚኖሩ በስተቀር ማናቸውንም እስራኤላዊ ያልሆኑ ሕዝቦችን ያካተተ አይደለም። እንዲያውም እስራኤላውያን ከሌሎች ሕዝቦች ተለይተው ለእግዚአብሔር እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው።

ኦሪት ዘጸአት  19፤5
አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ

ቃል ኪዳኑን ከእግዚአብሔር ጋር ያሰሩት ከአብርሃም ከይስሐቅና ከያዕቆብ በቀጥታ የተወለዱ እስራኤላውያን ናቸው። እናደርጋለን ብለውም ቃል የገቡት እነርሱ ናቸው። ቃል ኪዳኑ የታሰረበትንም ደም የተረጩት እነርሱው ናቸው። የቃል ኪዳኑም መታሰቢያ ሐውሎቶች የተሠሩት ለአሥራ ሁለቱ የእስራእል ነገዶች ነው።

ኦሪት ዘጸአት  24
3 ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ። እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። 4 ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ። 5 የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤልን ልጆች ጐበዛዝት ሰደደ። 6 ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው። 7 የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው እርሱም፦ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ። 8 ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ።

ይህ የብሉዩ ኪዳን አሕዛብን ማለትም እስራኤላዊ ያልሆኑትን እንደ ግብጽ፤ ኢትዮጵያ ወዘተ የመሳሰሉትን ሕዝቦች የማያካትት ወይም የማያቅፍ ኪዳን ነው። እንዲያውም እስራኤላውያን ከአሕዛብ ጋር እንዳይጋቡ የሚከለክል አሕዛብን ከኪዳኑ የሚያገልል (exclude) የሚያደርግ ኪዳን ነው።

ኦሪት ዘዳግም
73 ከእነርሱም ጋር አትጋባ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ።

ከዚህ በተጨማሪ ኪዳኑ ከአንድ ሕዝብ ብቻም ሳይሆን ከአንድ አገር ጋርም የቆራኘ ነው። ከእስራኤልን ሕዝብና እግዚአብሔር ለእነ አብርሃም ከሰጣቸው ከእስራኤል ምድር (ከነዓን) ጋር የተቆራኘ ኪዳን ነው።

ኦሪት ዘዳግም  4
37-38 አባቶችህን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ የጸኑትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊትህ እንዲያወጣ፥ አንተንም እንዲያገባህ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ እንዲሰጥህ፥ ከአንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ። 39 እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም ያዝ። 40 ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድርዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ።

ኦሪት ዘዳግም  4
1 አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ።

25 ልጆችን የልጅ ልጆችንም፥ በወለዳችሁ ጊዜ በምድሪቱም ብዙ ዘመን በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ በረከሳችሁም ጊዜ፥ በማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል ባደረጋችሁ ጊዜ፥ ታስቈጡትም ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር በሠራችሁ ጊዜ፥ 26 ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትገቡባት ምድር ፈጥናችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ አስመሰክራለሁ ፈጽሞም ትጠፋላችሁ እንጂ ረጅም ዘመን አትቀመጡባትም። 27 እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፥ እግዚአብሔር በውስጣቸው በሚያኖራችሁ በአሕዛብ መካከልም ጥቂቶች ሆናችሁ ትቀራላችሁ።

ማንን ነው በነዚህ ክፍሎች "እስራኤል ሆይ" እያለ እግዚአብሔር የሚናገረው? የሰጣቸውን የብሉዩን ኪዳን ትዕዛዝ ቢጠብቁ በሚሰጣቸው ምድር እንደሚባርካቸው የሚናገረው እነማንን ነው? ትዕዛዛቱን ባይጠብቁ ደግሞ ከሰጣቸው ምድር አውጥቶ እንደሚበትናቸው የሚናገረው እነማንን ነው? መልሱ የእስራኤልን ሕዝብ ነው የሚል ነው። ለሌላ ሕዝብማ እንደዚህ ያለ አገርና ከአገሩ ጋር የተቆራኘ ኪዳን አልተሰጣቸውም።

እነዚህ ክፍሎች ግልጽ እንደሚያደርጉልን የብሉይ ኪዳኑ ውል በሥጋ ከአብርሃም ከይስሐቅና ከያዕቆብ ከሚወለዱት ከእስራኤል ሕዝብና እግዚአብሔርም ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ከሚሰጣቸው ምድር ጋር የተቆራኘ ኪዳን ነው። የኪዳኑ በረክትም መርገሙም ከእስራኤል ሕዝብና እግዚአብሔር ከሰጣቸው ከከነዓን ምድር ጋር የተሳሰረ ነው። ይህ ኪዳን ግሪካውያንን ወይም ግብጻዊያንን ወይም ኢትዮጵያውንን የሚመለከት ኪዳን አይደለም። እንዲያውም የሚያገልል እንጂ። ስለዚህ በብሉይ ኪዳን የተካተተው የከነዓንን ምድር የመውረስ ጉዳይ ቢሆን ወይም በከነዓን ምድር መባረክ የአንድ ሕዝብና የአንድ አገር ኪዳን ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ከብዙ ግራ መጋባቶች ይጠበቀናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ከተማ ይኖሩ ለነበሩና በሥጋ እስራኤላዊ ላልሆኑ ለአዲሱ ኪዳን አማኞች በቀድሞው ኪዳን ምንም ቦታ እንዳልነበራቸው ሲናገር እንዲህ ይላል፦

ወደ ኤፌሶን ሰዎች  2
11 ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ 12 በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።

የቃል ኪዳኑ ይዘት


ማናቸውም ቃል ኪዳን የተመሠረተበት ውል ወይም ስምምነት አለው። ይህም ሁለቱ ቃል ኪዳን ተጋቢዎች ሊፈጽሙትና ሊጠብቁት ያለ ኃላፊነትን ሁለቱም በሚገባቸው ቋንቋ የሚገልጽ ነው።

ከላይ እንደተመለከትነው እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ይሄ ቃል ኪዳን ዋናው ውል ሕዝቡ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሕግጋት እንደሚጠብቁና ሕዝቡ ይሄን ካደረጉ ደግሞ እግዚአብሔር በበኩሉ አምላክ እንደሚሆናቸውና በሚሰጣቸው ምድር እንደሚባርካቸው የሚገልጽ ነው።

ኦሪት ዘጸአት 19
አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ።

ኦሪት ዘዳግም  4
40 ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ።

እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የገባው ይህ ቃል ኪዳን በረከት ብቻ ሳይሆን መርገምም ያዘለ ነው። ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ቢጠብቅ በረከትን እንደሚባረክና እንዲሁ ደግሞ ሕግጋቱን ባይጠብቅ እንደሚረገም የሚገልጽ ቃል ኪዳን ነው።

ኦሪት ዘዳግም  11
26 እነሆ፥ እኔ ዛሬ በፊታችሁ በረከትንና መርገምን አኖራለሁ 27 በረከትም፥ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰሙ 28መርገምም፥ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባትሰሙ፥ ዛሬም ካዘዝኋችሁ መንገድ ፈቀቅ ብትሉ፥ ሌሎችንም የማታውቋቸውን አማልክት ብትከተሉ ነው።

ኦሪት ዘዳግም  ምዕራፍ 28 ላይ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተካተተው በረከትና መርገም በዝርዝር ተቀምጦአል።

እንግዲህ የዚህ የብሉይ ኪዳን መሠረት ወይም የቃል ኪዳኑ ውል ዋና ይዘት እግዚአብሔር የሰጠው ሕግጋት ናቸው። በረከቱም መርገሙም እነዚህን ሕግጋት በመጠበቅ ወይም ባለመጠበቅ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

የታቦት ምንነት


ኦሪት ዘጸአት 25
1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2 ስጦታ ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ተናገር...
8 በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ። 9 እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት። 10 ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 11 በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። 12 አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። 13 መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። 14 ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ። 15 መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ። 16 በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ።

ቀድም ብለን እንዳየነው በዘጸአት 24 ላይ እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን ከገባ በኋላ በዚህ በዘጸአት 25 ላይ ደግሞ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ መካከል እንዲኖር ቤተመቅደስን እንዲሠሩለት ሲያዝ እንመለከታለን። ከቤተመቅደሱ ጋር አያይዞ ታቦትን ከግራር እንጨት እንዲሠሩና በታቦቱ ውስጥም እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን "ምስክር" እንዲያስቀምጡ ሲያዛቸው እንመለከታለን። የታቦቱ እንግዲህ ዋናው ዓላማ በዚህ ክፍል "ምስክር" ተብሎ የተጠራውን ነገር ማስቀመጫ እንዲሆን ነው። ስለዚህ ታቦቱ ይህ "ምስክር" ተብሎ ከተጠራው ነገር ጋር የተቆራኘ ነው ማለት ነው።

ኦሪት ዘጸአት31
18 እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው።

ኦሪት ዘዳግም4
ታደርጉትም ዘንድ ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን አሥሩን ቃላት ነገራችሁ በሁለቱም በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው።

ኦሪት ዘዳግም 10
ስብሰባ ተደርጎ በነበረበትም ቀን እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ የተናገራችሁን አሠርቱን ቃላት ቀድሞ ተጽፈው እንደ ነበረ በጽላቶቹ ላይ ጻፈ እግዚአብሔርም እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ። ተመልሼም ከተራራው ወረድሁ፥ ጽላቶችንም በሠራሁት ታቦት ውስጥ አደረግኋቸው እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ በዚያ ኖሩ።

እነዚህ ክፍሎች ደግሞ በታቦቱ ውስጥ የሚቀመጡትን "ምስክር" ተብለው የተጠሩትን ነገሮች ምንነት ግልጽ ያደርጉልናል። በዚህ ክፍል እንደምንመለከተው "ምስክር" ተብለው የተጠሩት አሥርቱ ቃላት "በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸው" ድንጋዮች ወይም ጽላቶች ናቸው። እነዚህ እግዚአብሔር ለእስራኤል ልጆች በታቦቱ ውስጥ እንዲያኖሩት የሰጣቸው አሥርቱ ቃላት የተጻፈባቸው ሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች እግዚአብሔርና የእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ቃል ኪዳን እንደተጋቡ የሚመሰክሩ ምስክሮች ናቸው።

ቀደም ብለን እንዳየነውም የዚህ ቃል ኪዳን የውል ስምምነት መካከለኛና የኪዳኑ በረከትም ይሁን መርገም መሠረት እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ የሰጠው ሕግ ስለሆነ እነዚህ አሥርቱ ትዕዛዛት የተጻፉባቸው ሁለት የድንጋይ ጽላቶች የብሉይ ኪዳኑ መሠረት ሕጉ እንደሆነና የእስራኤልም ሕዝብ በሙሉ አፍ እንደሚፈጽሙዋቸው ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን መግባታቸውን የሚያመለክቱ የብሉዩ ኪዳን ምስክሮች ናቸው።

ስለዚህ ታቦቱና በውስጡ የተቀመጡት የድንጋይ ጽላቶች የብሉዩ ወይም የቀድሞው ቃል ኪዳን ምስክሮች ስለሆኑ ከብሉዩ ኪዳን ጋር የተቆራኙና ተነጣጥለው ሊታዩም የማይችሉ ናቸው። ለዚህ ነው ታቦቱ ራሱ "የኪዳን ታቦት" ወይም "የምስክር ታቦት" እየተባለ የሚጠራው። ለብሉዩ ኪዳን መሠረትና ምስክር የሆኑትን ሕግጋት ስለያዘና ከብሉዩ ኪዳን ጋር የተቆራኘ ስለሆነ።

ኦሪት ዘጸአት
2633 መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ።

ኦሪት ዘጸአት
40በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ።

ኦሪት ዘዳግም
10በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ይሸከም ዘንድ፥ እርሱንም ለማገልገል በእግዚአብሔር ፊት ይቆም ዘንድ፥ በስሙም ይባርክ ዘንድ እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ የሌዊን ነገድ ለየ።
3125 ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዘ

እንግዲህ ከላይ ባጭሩ እንደተመለከትነው ታቦት ከነስሙ "የቃል ኪዳን ታቦት" ነው። ማለትም ከአንድ ቃል ኪዳን ጋር የተቆራኘ ስለዚያ ቃል ኪዳን የሚመሰክሩትን የምስክር ጽላቶች የያዘ ምስክር ነው። ይህም ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በሲና ተራራ የገባው የብሉዩ ኪዳን ነው። በታቦቱ ውስጥ ባሉት በምስክሩ ጽላቶች ላይ የተጻፉት አሥርቱ ቃላት ከብሉይ ኪዳኑ የማይነጣጠሉ እንደሆኑ ሁሉ የኪዳኑም ታቦት ከብሉይ ኪዳን ጋር የተቆራኘና የማይነጣጠል ነው። የሚመሰክረው ስለ ብሉይ ኪዳኑ ነውና።

ታቦት እንግዲህ ከግራር እንጨት የተሠራ በመቅደሱም በውስጠኛው ክፍል ማለትም በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የሚቀመጥ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው የቀድሞው ወይም የብሉይ ኪዳን ምስክር የሆኑትን የድንጋይ ጽላቶች የያዘ የብሉዩ ኪዳን ምስክር ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ታቦት ሲጠቀስ እንግዲህ ያን በሲናና ተራራ የተፈጸመውን ቃል ኪዳን የሚያመለክት ነው። ይህም የቃል ኪዳኑ ተጋቢዎች የሆኑትን እግዚአብሔርንና የእስራኤል ሕዝብን እንዲሁም የቃል ኪዳኑ የውል ስምምነት የሆነውን ሕጉን የሚያስታውስ ነው።


1 comment: